የአማርኛ ግጥሞች

እስከመቼ?
እስከመቼ?
እስከመቼ በጉልበት መነጣጠቅ
ሥልጣንን በትንቅንቅ?
እስከመቼ በሽኩቻ
ሀገርን ማድረግ ገወቻ?
እስከመቼ መሆን ሙጫ
ያለዲሞክራሲ ምርጫ?
እስከመቼ ወንጃ ወንጃ
መፍትሔ መሻት በጠበንጃ?
እስከመቼ…?
እስከመቼ…?
እስከመቼ ወተምተም ወተምተም
አረጋግዞ ጥላቻና ቂም?
እስከመቼ እንጎድ እንጎድ
በመብረቅ ድምፅ በነጎድጓድ?
እስከመቼ ቃሰንተኛ
የሙስና ሱሰኛ?
እስከመቼ ማቶንቶን
ያለነፃነት መታፈን?
እስከመቼ መርገጥ ጭቅጫቅ
ያለ ፍትህ መንቦራጨቅ?
እስከመቼ…?
እስከመቼ…?
እስከመቼ መጠላለፍ
እያመጹ ጥሎ ማለፍ?
እስከመቼ ምቀኝነት
በቀልና መጥፎ ቅናት?
እስከመቼ አምባገነን
እየሾሙ የራስ ወገን፣
እየሻሩ የራስ ሕግን?
እስከመቼ ማሰብ ሴራ
የማይጠቅም ክፉ ሥራ?
እስከመቼ…?
እስከመቼ…?
እስከመቼ ጌታ፣ ሎሌ
መፈናከት በብርሌ?
እስከመቼ በቅራኔ
መወናጀል በኩነኔ?
እስከመቼ እሳት መጉረስ፣
እሳት መድፈን፣ እሳት መላስ?
እስከመቼ ቀዳዳ ቤት
በፉክክር የማይዘጉት?
እስከመቼ “ነፃ አውጭ ግምባር”
ነፃ የማያወጣ ግርግር?
እስከመቼ አለመስማማት
ለራስ ብቻ ወየው ማለት?
እስከመቼ…?
እስከመቼ…?



አገሬ ውበት ነው
ለምለምና ነፋስ የሚጫወትበት
ጸሃይ የሞላበት፣ ቀለም የሞላበት።
አገሬ ቆላ ነው፣ ደጋ ወይና ደጋ
እዚያ ብርሃን አለ ሌሊቱ ሲነጋ።
አገሬ ተራራ ሸለቆ ረባዳ
አገሬ ጅረት ነው ገደልና ሜዳ።
ውሸት ነው በበጋ ጸሃይ አትፋጅም
ክረምቱም አይበርድም፣
አይበርድም፣ አይበርድም።
አገሬ ጫካ ነው
እንሰሳት አራዊት የሚፈነጩበት
በወጥመድ ሳይገቡ ሳይነካቸው ጠላት።
እዚያ አለ ነጻነት።
በሃገር መመካት፣
በተወላጅነት፣
በባለቤትነት፣
እዚያ አለ ነጻነት።
አገሬ ሃብት ነው።
ጎመኑ ስብ ጮማ፣ ቆሎ ክትፎ ስጋ
ድርቆሹ ፍትፍት ነው፣ ቃሪያው ሙክት ሠንጋ።
ጠጁ ነው ወለላ
ከኮኛክ ይነጥቃል የመንደሩ ጠላ።
እህሉ ጣዕም አለው እንጀራው ያጠግባል
በዓሉ ይደምቃል፣
ሙዚቃው ያረካል፣
ጭፈራው ዘፈኑ ችግርን ያስረሳል።
እዚያ ዘመድ አለ።
ሁሉም የናት ልጅ ነው፣
ሁሉም ያባት ልጅ ነው፣
ጠላትም አንዳንዴ ይመጣል መቃብር
ባለጋራም ቸር ነው “ያገር ልጅ ሲቸገር” ።
ገነት ነው አገሬ።
ምነው ምን ሲደረግ !
ምነው ! ለምን ! እንዴት !
ዘራፊ ቀማኛ ምቀኛ ወንበዴ
ጥርኝ አፈር በጁ ስንዝር ወሰን አልፎ
የተቀደሰውን ያፍሪቃ ላይ ደሴት
ባያገኝ ለማርከስ ጠላት ይመኝ እንዴት።
እምቢኝ አሻፈረኝ !
አሻፈረኝ እምቢ !
መቅደስ ነው አገሬ፣
አድባር ነው አገሬ።
እናትና አባት ድኸው ያደጉበት
ካያት ከቅደመ አያት የተረካከቡት
አፈር የፈጩበት፣
ጥርስ የነቀሉበት።
አገሬ ዓርማ ነው የነጻነት ዋንጫ
በቀይ የተጌጠ ባረንጓዴ ብጫ።
እሾህ ነው አገሬ፣
በጀግናው ልጅ አጥንት የተከሰከሰ
ጠላት ያሳፈረ አጥቂን የመለሰ።
አገሬ ታቦት ነው መቅደስ የሃይማኖት
ዘመን የፈተነው በጠበል በጸሎት።
ለምለም ነው አገሬ፣
ውበት ነው አገሬ፣
ገነት ነው አገሬ።
ብሞት እሄዳለሁ ከመሬት ብገባ
እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ።
ስሳብ እሔዳለሁ ቢሰበርም እግሬ
አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ አገሬ።
አለብኝ ቀጠሮ
ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ። 

ገብረክርስቶስ ደስታ።

ድምጽ አልባ ፊደላት

ፀጉሩን አንጨብሮ ፂሙን አጎፍሮ
ጥግ ተቀምጦ ለሚታየኝ ወጣት
ሂድና ታዘዘው ስጠው አንድ ድራፍት
ቅዳለት ደብል ጂን ሃሳቡን ይርሳበት
በፂሙ መጎፈር በፀጉሩ መንጨብረር
ቁጥር ፈታ በሚል በግንባሩ መስመር
ይታየኛል ቃንቃ ይታየኛል ነገር
እዛም ከጨለማው ብቸኝነት ውጣት
ሲጋራዋን ይዛ ለቆመችው ወጣት 
ሂድና ታዘዛት የሚጠጣ ስጣት 
ምጋ በተፋችው በጭሶቹ መሃል
ሴትነት ሲበደል እህትነት ሲጣል
እናትነት ሲጎድል
ይታየኛል ቃንቃ ይታየኛል ፊደል።

ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን